ፀረ ሰላም ኃሎችን ከብሄርና ከሐይማኖት ተቋማት ልንለያቸው ይገባል

0
521

ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ የብሄር ብሄረሰቦችና የሌሎችም ልዩነቶች  የእኩልነት  ጥያቄ  በህግ መንግስቱ ከተመለሰ በኋላ እንኳን ልዩነቶቹን እንደ መደበቂያ ምሽግ የመጠቀም ስትራቴጂ ቀጥሏል፡፡ በተለይ በተለይ ያኮረፉ ፖለቲከኞች፣ ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ሽብርተኞችና ሌሎችም ጸረ ሠላም ኃይሎች ለሁሉም ዜጎች የተዘረጋው ሠላማዊውና ህጋዊው መንግድ አላዋጣ ሲላቸው ህገ ወጡን መንገድ ለመጠቀም እንደ ምሽግ የሚጠቀሙት ሐይማኖትንና ብሄርን ነው፡፡

   ይህን አካሄዳቸውን አደገኛ የሚያደርገው ሐይማኖትን ከሐይማኖት፤ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት ይህች ሀገር ማባሪያ ወደ ሌለው ትርምስ ውስጥ እንድትገባም ስለሚያደርግ ነው፡፡ በሐይማኖቶችና በብሄሮች መካከል የሚነሳ ግጭት ደግሞ ከራሳችንም ሆነ ከዓለማችን ታሪክ እንደምንረዳው አሸናፊና ተሸናፊ የሌለው እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ የሚሄድ አደገኛ ነገር ነው፡፡

   እነዚህ ራስ ወዳድ የጥፋት ኃይሎች ሲመቻቸው የሐይማኖት ተቆርቋሪ በመምሰልና በህገ መንግስቱ የተመለሰውን ጥያቄ እንዳልተመለሰ በመስበክ በርካቶችን በስሜታዊነት በእሳት እንዲማገዱ አድርገዋል፡፡ በዚህ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ የአንዱ ብሄር ተቆርቋሪ በመምሰልና ሌላውን በመኮነን የዋሆችን ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ በማድረግ ለዚህች ሀገር ብዙ መልካም ነገር ማድረግ የሚችሉ ዜጎችን በከንቱ እንዲሞቱ አድርገዋል፡፡

   አዲሱ የለውጥ ጉዟችን የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለበጎ ተግባር ከማዋል ይልቅ ለዚሁ እኩይ ተግባራቸው እየተጠቀሙበት በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች ግጭትና ሁከት እንዲፈጠር አጥብቀው እየሠሩ ናቸው፡፡ በዚህም መንግስትን ከህዝብ በማቀያየም ለህዝብና መንግስት አላስፈላጊ የሆነ የቤት ሥራ በመፍጠር ለራሳቸው ግን ዕድሜያቸውን የሚያራዝሙበትን ዕድል እያመቻቹ ናቸው፡፡

   እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በዚሁ እኩይ ግባራቸው የሚቀጥሉ ከሆነ በተያያዝነው የለውጥ ጉዞ ላይ ጥላ ማጥላታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ እንደህዝብና መንግስት ለዘመናት ጸንቶ የቆየውን የጋራ ዓላማ በማንግብ እነዚህን መሠሪና የጥፋት ኃይሎች ከሐይማኖት ተቋማትና ከብሄር በመለየት በህግ ፊት ልናቀርባቸው ይገባል፡፡

   የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       23/02/2011ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here