ለውጡ ያመጣውን ጥሩ ዕድል ልንጠቀምበት ይገባል

0
632

በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለፈውን የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ በቅጤ ያገናዘበ እና ብልሀት የተሞላበት የለውጥ አቅጠጫ መከተል የጀመርነው አሁን ነው፡፡ ይህን አዲሱን የለውጥ ጉዞ ለየት የሚያደርገው መንግስት ኃይልን  የመጠቀም አቅሙና ዕድሉ እያለው እሱ አያስፈልግም በማለት በፍቅርና በይቅርታ እንደመር  ብሎ በውጪም በውስጥም ላሉት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ጥሪ ያቀረበበት የለውጥ ጉዞ መሆኑ ነው፡፡

            ከዚህ በፊት  ሀገሪቱን የመምራት ዕድል በተለያዩ መንገዶች ያጋጠሟቸው ሥርዓቶች የራሳቸው ጠነካራ ጎን ቢኖራቸውም በሀገር ውስጥ ችግርን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ግን ኃይልን መጠቀም ነበር፡፡ ይኼ ደግሞ በጣም ቀላሉና ደካማ ሥርዓቶች ሲጠቀሙበት የነበረ ውጤቱም የዜሮ ድምር አካሄድ ነው፡፡ በተለይ የህግ የበላይንትን በራሳቸው ፍላጎትና መንገድ ባልተመጣጠነ ኃይል ለማስፈን የሄዱበት የመግድል፣ የማሰርና የማፈናቀል አካሄድ በሂደት ከህዝብም ከሌሎች ዓለም አቀፍ የዴሞክራሲ ተቋማት አራርቋቸዋል፡፡

             አሁን ደግሞ በሀገር ውስጥም በውጪም በግፍ የታሰሩ እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትክክለኛ ነጻነቱ ተጠብቆለት መተኪያ ሌላት ሀገሩ የራሱን አስትዋጽዖ እንዲያበርክት ዕድሉ ተመቻችቷል፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሳይገደብ እንዲሰፋና ሁሉም በሚደግፈው ሀሳብ ሥር ተደራጅቶ የተሸለ አማራጩን ለህዝብ በማቅረብ የመመረጥ ዕድሉን ካገኘ በሠላማዊ መንገድና ሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲጠቀምበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

                 እነዚህ ዕድሎችና ለውጡ ያመጣቸው ሌሎች ሌሎች ትሩፋቶች ከማንም በላይ የሚጠቅሙት ህዝቡን ነው፡፡ መንግስት ቀላሉን የማሰርና የመግደል አካሄድ በመኮነን በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ውይይት በፍቅርና በይቅርታ እንደመር ብሎ ጥሪ በማድረጉ አላስፈላጊ ጫና ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ እኛም እንደዜጋና የአንዲት ሀገር ህዝብ ሠላማዋዊውን መንገድ እንጂ የጠብንና የብጥብጥን መንገድ ልንከተል አይገባም፡፡

                 ካሳለፍናቸው ውድቀቶቻችን ጊዜ ሳንወስድ ቶሎ ተምረን በፍቅርና በይቅርታ እንደመር፡፡ ምክኒያቱም ይህን የለውጥ ጉዞ መከተል የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነውና፡፡ ከመበታተናችንና እርስ በእረስ ከመጨራረሳችን በፊት እንዲህ ዓይነቱ ሠላማዊውና ወደ ብልጽግና የሚመራን የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ በመግባታችን በጣም ዕድለኞች ነን፡፡

               ይህን ዕድል በአግባቡ ልንጠቀምብት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን ስናውቀውም ሆነ ሳናውቀው የለውጡን ጉዞ እያደናቀፍን የለውጡ ጉዞ ቢዘገይ ወይም ቢቀለበስ ሊመጣ   የሚችለው ጉዳት አሁን ከምንገምተው በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከስሜታዊነትና ከሀሰተኛ መረጃዎች በመራቅ ቆም ብለን ልናስብ የሚገባው አስቀድሞ አሁን ነው፡፡

            የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                                   19/02/2011ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here