ለውጡን የማስቀጠል እና ያለማስቀጠል ጉዳይ

0
619

በዚህ ትውልድ ፊት የተደቀነው የቤት ሥራ በእጅጉ ከባድ እና መስዋዕትነት የሚያስከፍል ቢሆንም የቤት ሥራውን የመወጣትና ያለመወጣት  ጉዳይ ግን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ የተጀመረው በፍቅርና በይቅርታ የመደመር ጉዞ ለውጥ ገና ከጅምሩ እንቅፋቶች እና ተግዳሮቶች የበዙበት ቢሆንም ከሀገር ውስጥ እስከ ዲያስፖራ ከዛም አልፎ ጎረቤት ሀገሮችን ሳይቀር በርካቶችን ከጎኑ ለማሰለፍ ችሏል፡፡

       የለውጥ ጉዞውን አሁን የጀመርነው ከበርካታ ዓመታት  የእርስ በእርስ ግጭት በኋላ በመሆኑ ጉዟችን አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው፡፡ ምክኒያቱም የበደለ ከልቡ ይቅርታ ጠይቆ ይቅር መባል አለበት፡፡ የተበደለ ደግሞ ይቅርታ አድርጎ መካስ አለበት፡፡

       ስለዚህ  አሁንም በተግባር አንደምናየው የለውጥ ጉዟችን ስጋቶችና ተግዳሮቶች እንዳሉበት በግልጽ በተግባር እያየን ነው፡፡ እነዚህ ሥጋቶችና ተግዳሮቶች የሚመነጩት ከሁለት ዋና ዋና መነሻዎች ነው፡፡ እነዚህን የሥጋትና የተግዳሮት ምንጮች በሚገባ ተገንዝቦ የጀመርነው ለውጥ እንዳይደናቀፍ ሁላችንም በያለንብት የቤት ሥራችንን መወጣት ይገባናል፡፡

       የመጀመሪያውና ዋናው የሥጋት ምንጭ ለውጡ በዚሁ ከቀጥለ በዚህች ሀገር በተጨባጭ የሚመጣው ውጤት ጥቅማቸውን የሚያሳጣቸው እና የሚያሳስባቸው ኃይሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከሀገር ውጪ እና በሀገር ውስጥ የተሳሰሩ በመሆናቸው በጀት ተመድቦላቸው እና ተልዕኮ ተሰጥቷቸው እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡

   የለውጡን ጉዞ ለማሰቆም ሲሉ ለውጡን የሚመሩ በሳል መሪዎችን ለመግደል ቅጥር ነፍሰ ገዳይ አስከ መቅጠር የሄዱበትን እኩይ ሴራ ያከሸፈው የህዝብ ርብርብ ነው፡፡ ብሄርን ከብሄር በማጋጨት በዚች ሀገር መረጋጋት እንዳይኖር ያሴሩትን ሤራም  ያከሸፈው ህዝቡ ነው፡፡ ይህ የህዝብና የመንግስት ቁርጠኝነት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

       ሌላውና ሁለተኛው የለውጥ ጉዟችን ሥጋት የለውጡ ምንነት ያልገባውና የአፍራሽ ኃይሎች የበሬ ወለደ የፈጠራ ወሬ ሰለባ የሆኑ ኃይሎች ናቸው፡፡ አነዚህ ኃይሎች የጀመርነው የለውጥ ጉዞ በዚህች ሀገር በተጨባጭ የሚያመጣውን ትውልድ ተሸጋሪ ውጤት ባለመረዳታቸው በተደጋጋሚ የአፍራሽ ኃይሎች መጠቀሚያ ሲሆኑና ከአንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ የማይጠበቅ ተግባር ሲፈጽሙ አይተናቸዋል፡፡

       እነዚህን ሳይሰለቹ በትዕግስት የማስተማርና ወደ ትክክለኛው የለውጥ መስመር ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ሥራው ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ከቤተሰብ እስከ ትምህርት ቤት፤ ከባለድርሻ አካላት እስከ ሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ሊረባረቡበት የሚገባ ሥራ ነው፡፡

      ለውጡን የማስቀጠል እና ያለማስቀጠል ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       16/02/2011ዓ.ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here