አዲስ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር የሰላም እሴትን ከመገንባት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተጠቆመ

0
932

በተለያዩ ጊዜያት ሀይማኖት ብሔርና ማንነትን ሽፋን በማድረግ የሚከሰቱ ግጭቶች የህዝቦችን ሰላማዊ የኑሮ እንቅስቃሴ በማወክ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ሲዳርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ተፈጥሮአዊ ባህሪ ያለውን ግጭት ለምን ተፈጠረ ብሎ መጠየቅ ባይቻልም በዘለቄታነት ችግርን ለመፍታት ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያስኬድ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

መጋቢ ይታገሱ ኃ/ሚካኤል በኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የክልል ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ እንደሚሉት ሰላም ከሌለ ትምህርት ፣ ጤና ፣ ግብር እንዲሁም እንቅስቃሴ የለም፡፡ሰላም ሲኖር ነው ሁሉንም ማሳካት የሚቻለው ስለሆነም አዲስ የተቋቋመው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለሁሉም መሰረት ነው ብለዋል፡፡

             በኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ ሀይማኖት ተቋማቶች የጋራ የሚያደርጓቸው ጉዳዮች እንዳሏቸው የገለፁት መጋቢው እነዚህ አስተምህሮቶች ደግሞ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍትህና ይቅርታ የመሳሰሉት በጎ ምግባራት ናቸው ብለዋል፡፡ ማህበረሰቡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ልዩነት የለውም ያሉት መጋቢ ይታገሱ ብዝሃነት ተፈጥሮአዊ እንጂ ሰው ሰርቶ ያመጣው ባለመሆኑ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ሰላምን አስጠብቆ መኖር የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

እንደተቋም በተያዘው በጀትአመት የሀገሪቱን ህዝብ ቁጥር አብላጫውን በሚይዙት ሴቶችና ወጣቶች ላይ ጥራትና ውጤት ያለው ስራ ለመስራት ማቀዳቸውን የገለፁት መጋቢ ይታገሱ፤ሴቶችና ወጣቶች የሰላምና የአብሮነት መሣሪያ እንጂ የአፍራሽና የአጥፊዎች ሰለባ እንዳይሆኑ እስከ ቀበሌ ድረስ መዋቅራቸውን በመዘርጋት የሰላም እሴት ግንባታ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ጠቁመዋል ፡፡

አቶ መሱድ አደም በኢትዮጵያ ሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ በበኩላቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ ግጭቶችን በመፍታት ማህበረሰቡ በሰላምና በመከባበር እንዲሁምበአብሮነት የመኖር ባህሉን አዳብሮ እንዲሄድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱየሆነ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ሰዎች ከሀይማኖት ተቋማት በመራቃቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭቶች እንዲበራከቱአይነተኛ መንስኤ መሆኑን የተናገሩት አቶ መሱድ ራስ ወዳድነት፣መገፋፋት፣በዘር፣በብሔርና በጎሳ መከፋፈልም የሚመጣው ሰዎች ከቤተ-እምነት እየራቁ በሄዱ ቁጥር ስለሆነ ይህንን ለማስቆም ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ለምእመኑ መልካም ስነምግባርን በማስተማር ሀገሪቱ እየገባችበት ካለው ማህበራዊ ቀውስ ለመታደግ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here