በድሬ ጉዳይ ላይ ጠያቂ እና ሞጋቾች ልንሆን ይገባል

0
673

በመንግስት እና በህዝብ መካከል ያለው የሠመረ መስተጋብር እንዲቀጥል ሁለቱም በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚጠይቁ፣ የሚወያዩ እንዲሁም መፍትሄን በጋራ የሚያፈላልጉ መሆን አለባቸው፡፡ በተለይ ህዝብ የሉዓላዊ ስልጣን ሁሉ ባለቤት በመሆኑ መንግስትን የመከታተል፣ የመደገፍ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ በአግባቡ የመጠየቅ መብትም ባለቤት ነው፡፡

ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ የሆነ መንግስታዊ ሥርዓት ህዝቡ በሁሉም ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በንቃት የሚሳተፍ ብሎም ጠያቂ እና ሞጋች ሲሆንለት ደስ ይለዋል፡፡ አሁን በሀገራችን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመለክተው ያለው መንግስታዊ ሥርዓት ልማታዊ እና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ለዚህ ብዙ መገለጪያዎችን ማየት ይቻላል፡፡ ከሁሉ በላይ ለዚህ ምስክሩ ግን በብዙ ትግል እና መስዋዕትነት የጸደቀው ህገ-መንግስታችን ነው፡፡

ስለሆነም እንደ ድሬደዋ ነዋሪ ህገ-መንግስቱ ባጎናጸፈን መብት ተጠቅመን ስለ ድሬደዋ ጉዳዮች በሙሉ በያገባናል እና በባለቤትነት ስሜት በነቃት ልንሳተፍ ይገባል፡፡ መንግስትም እንደሚያምነው በዚህ በምንገኝብት ዘመን በተከታታይ በተሠራው የግንዛቤ ሥራ በሀገሩ ጉዳዮች ላይ ጠንካራ፣ ጠያቂና ሞጋች ማህበረ-ሰብ ተፈጥሯል፡፡ በነጻነትና በሀቅ ላይ የተመሠረቱ መረጃዎችን በመጠቀም የልማት፣የመልካም አስተዳደር እና የሠላም ጉዳዮችን አንስቶ በመጠየቅ መወያየት ይቻላል፡፡

የተሳሳቱ፣ ምንጫቸው የማይታወቅ እና የተጋነኑ መረጃዎችን ይዞ በህዝብ መሀል በመንዛት የመንግስትን ሥራ ማንኳሰስ ግን  የትም አያደርስም ፤ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ምክኒያትም ዕውነታው እና ሀቁ እየታወቀ ሲሄድ አውቀውም ሆነ ሳያወቁ እንዲህ ዓይነቱን ሀገርን እና ወገንን የሚጎዳ ተግባር የሚፈጽሙ ኃይሎች የኋላ ኋላ ማፈራቸው አይቀሬ ነው፡፡

ራሱን ለማረም ዝግጁ የሆነ እና ከህዝብ ምንም ሳይደብቅ በግልጽነት ያቀደውን እያወያየ የሚሠራ የመንግስት ሥርዓት ባለቤቶች ሆነናል፡፡ ስለሆነም አሉባልተኞችንና የጥፋትን መንገድን እንደ ጀብድ የሚከተሉትን በጋራ ተልዕኳቸውን ልናከሽፍ ይገባል፡፡

ሠላሙ፣ልማቱ፣መልካም አስተዳደሩ እና ሌሎችም ለድሬ ይበጃሉ የምንላቸው አጀንዳዎቻችን ግን የጋራዎቻችን ናቸው፡፡ ሁላችንንም ይመለከተናል፤ ያገባናል በሚል የባለቤትነት ስሜት ተቀራርበን ልንወያይባቸው ይገባል፡፡ ሁላችንም ስለ ድሬ ጉዳይ ያለንን መረጃ እናጥራ፤ እንጠይቅ፤ እንሞግት፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         03/03/2011ዓም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here