ነፃነት ሰንደቅ ዓላማ ነፃነት

0
634

ሰንደቅ ዓላማ  የአንድ ሀገርና ህዝብ የነፃናትና የሎዓላዊነት ዓርማ፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ሲውለበለብ ሰንደቅ ዓላማው የወከለው ሀገርና ህዝብ ነፃና ሉዓላዊ መሆናቸውን የሚያሳይ አስገራሚና የተለየ ስሜት የሚፈጥር ክስተት ነው፡፡ ለዚህም ነው በዓለም መድረኮች አትሌቶቻችን አሸንፈው ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ ሲውለበለብ እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው የሚያነቡት፡፡ በእነሱ ምክኒያት  በዓለም አደባባይ ሰንደቅ ዓላማው    ከፍ ብሎ መውለብለቡ የፈጠረባቸው ልዩ ስሜት ነው ያስለቀሳቸው፡፡

         ለመሆኑ አድዋ ላይ እነዚያ ዓለምን ጉድ ያስባሉ ጀግኖች አባቶቻችን ለአንዲት ነፍሳቸው ሳይሳሱ እስከ አፍንጫው ታጥቆ የመጣውን ወራሪ የኢጣሊያ ጦር የገጠሙት ለምንድነው? በገዛ ሀገራቸው ነፃነታቸውንና ሉዓላዊነታቸውን ገፎ ዓይናቸው እያየ የባዕድ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ ከሚውለበለብ ሞትን ስለመረጡ ነው፡፡

       እነዚያ ጀግኖች አባቶቻችን ለሰንደቅ ዓላማው ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር በተግባር ያሳዩበት ሂደት እስከ ዛሬ ድረስ ከሀገር አልፎ ለበርካታ የአፍሪካ ሀገራትና ለዓለማችን በሙሉ እንደ ተምሳሊትና ዓርአያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህን አኩሪና ከመቃብር በላይ ሲዘከር የሚኖር የጀግንነት ተግባር ከመዘከር ባለፈ በእነሱ ጫማ ተተክተን እኛም ባለተራዎች ነንና ለሰንደቅ ዓላማው ክብር የሚጠበቅብንን ሁሉ  ማድረግ ይገባናል፡፡

       አሁን እዚህም እዚያም ስለ ሰንደቅ ዓላማው የሚታዩ ክርክሮችና የሀሳብ ልዩነቶች ከደረስንብት የአስተሳሰብ ዕድገትና እየተፈጠረ ካለው ትክክለኛው የዴሞክራሲ ድባብ እንዲሁም  ነጻነት ሳቢያ የመጡ ናቸው፡፡ ስለሆነም እየመጣ ያለው ለውጥ አካል አድርገን እንጂ እንደ መጥፎ ክስተት ባንወስዳቸው ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ በሰከነና ትዕግስት በተሞላበት አካሄድ እየተወያየን ልዩነቶቻችንን እያጠበብን ወደ ጋራ መግባባት መድረሱ  የተሻለ አማራጭ ነው፡፡

       የጋራ መግባባቱ እስኪመጣ ድረስ ግን በህገ መንግስታችን የጸደቀውንና አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሰንድቅ ዓላማ ማክበር እና በጨዋ ደንብ መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ከሰንደቅ ዓላማው ጀርባ ከመቶ ሚሊየን ህዝብ በላይ ስላለ በጠብና በዓመጽ ሰንደቅ ዓላማውን ለመቀየር መሞከር አላስፈላጊ መስዋዕትነትና የኋላ ኋላ የሚጸጽት ጥፋት እንጂ ውጤት አይኖረውም፡፡

       ስለዚህ ከስሜታዊነትና ከአላስፈላጊ ጠብ ርቀን ለውጡ ያመጣውን መልካም አጋጣሚ በብልሀት ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ የአንድ ትውልድ ጉዳይ አይደለም፡፡ ትውልድ ሁሉ በየተራው አሻራውን ያኖረበት በሂደትም ታሪካዊ አንድነቱን ያሳየበት ነው፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                     ድሬዳዋ

                                                       02/02/2011ዓ.ም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here