ተክክለኛና ምክኒያታዊ እንድንሆን መረጃን ከትክክለኛ ምንጭ እንውሰድ

0
606

ማንኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው በንቃት ተሳትፎ ለሀገሩ አንዳች አስትዋጽዖ ማበርከት ይፈልጋል፡፡ ይህንን የተቀደሰና ከሀገር ፍቅር የሚመነጭ ፍላጎት ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ እና ቀጣይ እንዲሆን ለማድረግ ትክክለኛና ከምንጩ የተቀዳ መረጃ ያስፈልገናል፡፡ ምክኒያቱም ስለራሳችንም ሆነ ስለሀገራችን ትክክለኛና ተገቢ ውሳኔ ለመወሰን በትክክለኛ መረጃ ላይ መመስረት ስለሚገባ ነው፡፡

አሁን እንደሀገር  እና እንደ ህዝብ የምንገኝበት  ተጨባጭ ሁኔታ  እንደሚያመላክተው  ከሆነ እያነዳንዱ ዜጋ በሰከነና ማስተዋል በተሞላበት መንግድ በምክኒያት መደገፍና በምክኒያት መቃወም ወይም መንቀፍ እንደሚገባው ነው፡፡ ይህ በእጅጉ የሚጠቅመው በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ይህንን የለውጥ ሂደት   እንደ አንድ መላካም ዕድል በመጠቀም ለሀገር እንዲጠቅም ለማድረግ  ነው፡፡

የምንገኝበት ወቅት በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ትክክለኛው የዴሞክራሲና የነጻነት ድባብ እየታየ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች በሀገር ውስጥ ያሉትም ሆኑ በውጪ የሚገኙት ወደ ሀገር ተሰባስበው ሀሳባቸውንም ሆነ ፍላጎታቸውን ለህዝቡ በነጻነት እንዲያሳውቁ ከበቂ በላይ ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዜጎችም የፈለጉትን ሰምተው እንዲደግፉና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ እንዲነቅፉ የፖለቲካ ምህዳሩ በግልጽ በዓይን እስኪታይ እንዲሰፋ ተደርጓል፡፡

ለሀገር የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የመወሰን ስልጣኑን ህገ መንግስታችን ለህዝብ ነው የሰጠው፡፡ ስለሆነም እንደ ህዝብ ይህን ለማድረግ እንደ ፌስቡክና ዩቲዩብ በመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚለቀቁ አሉባልታና የፈጠራ ወሬዎች ላይ ሳይሆን መረጃዎችን ከትክክለኛ ምንጭ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያዎች በፈጠራ ወሬዎቻቸው ሀገርን ሊያፈርሱ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ በበቂ ማስረጃዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በዓለማችን አንዳንድ ሀገሮች ላይ የታየው እውነታም ይኸው ነው፡፡ በተለይ ወጣቱን ስሜታዊ በማድረግ የገዛ ወገኑንና ሀገሩን እንዲጎዳ የተደረገውም በነዚሁ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚለቀቁ የአሉባልታና የሀሰት ወሬዎች በመጠቀም ነው፡፡

ስለሆነም ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ከዚህ በኋላ ወጣቱም ሆነ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ስሜታዊ ሳንሆን ተረጋግተን በትክክለኛ መረጃ ላይ በመደገፍ በምክኒያት ልንደግፍና ልንነቅፍ ይገባል፡፡ ምክኒያቱም መረጃን ከምንጩ መውሰድ ለውጡን ለማስቀጠልና ሀገርን ለመገነባት ወሳኝ በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለንና፡፡

የመንግስት ኮዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                      ድሬደዋ

                                                                         05/02/2011ዓም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here