የህግ የበላይነትን በህጋዊ መንገድ ማረጋገጥ ለዜጎች መከበር ዋስትና ነው

0
713

በዓለማችን በየትኛውም ሀገር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እገዳ የማይጣልባቸው ሰብዐዊም ሆኑ ዴሞክራሲያዊ  መብቶች  የሉም፤ አይገኙምም፡፡ ሁሉም የመብት ዓይነቶች በአጠቃቀማቸው  ላይ  የህግ ጥሰት ሲታይባቸው በህጋዊ መንገድ እገዳ ሊጣልባቸው ይችላል፡፡ የትኞቹንም መብቶቻችንን ስንጠቀም የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግስትና ሌሎች ዝርዝር ህጎችን ፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን  የምንጥስ ከሆነ መብቶቹ መብቶች መሆናቸው ይቀርና ወንጀሎች ይሆናሉ፡፡

እንግዲህ ይሄኔ ነው የህግ የበላይነት በእጅጉ የሚያስፈልገው፡፡ አለበለዚያ ግን ዜጎቿ በትንሽ ትልቁ በማንም የሚደፈሩባት አሷም በዓለም የተናቀች ሀገር ባለቤት መሆናችን አይቀሬ ነው፡፡ ዜጎቿ የሚከበሩባትን ሀገር ማንም መናቅ አይችልም፡፡ ዜጎቿ የሚናቁና የሚደፈሩባትን ሀገር ግን ማንም አያከብርም፡፡

የህግ የበላይነቱ ደግሞ ሲተገበር  ዓላማው  በህጋዊ መንገድ ብቻ  በህገ መንግስቱ የተጎናጸፍናቸውንም ሆነ ሰው ሆነን በመፈጠራችን የተጎናጸፍናቸውን  መብቶቻችንን  መገደብ ሳይሆን የተፈጠረውን የህግ ጥሰት ማስተካከልና የሌሎችን መብቶች ማስከበር ነው፡፡

ባጠቃላይ  አነጋገር መብቶቻችንን በህገ ወጥ መንገድ የምንጠቀም ከሆነ ለሌሎች ዜጎች መብቶችና  ለሀገር ደህንነት ሲባል እንነጠቃለን ማለት ነው፡፡ በየትኛውም የህግ መድረክ ዴሞክራሲያዊና ሰብዐዊ መብቴ ነው ብለን መጠየቅ እንዳንችል በህጋዊ መንገድ ዕገዳ ይጣልብናል፡፡

የመናገርና የመጻፍ መብቶቻችንን በተግባር ስንለማመድ የሌሎችን ክብር፣ ስብዕናና መብቶች የምንጥስባቸው ከሆነ መብቶች መሆናቸው ይቀርና ወንጀል ይሆናሉ፡፡ ህጉ ደግሞ ወንጀለኛን በህጋዊ መንገድ የመቅጣት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ማንነታችንን ለማስከበር የሌሎችን  ማንነት መደፍጠጥ አይቻልም፡፡

በህይወት የመኖር መብት በእርግጥ በማንም አይሰጥም ለሌሎች ዜጎች በህይወት መኖር ስጋት ስንሆን ግን ይህንን ሰብዐዊ መብት ልናጣው የምንችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከቦታ ቦት የመንቀሳቀስ መብታችንም በተመሳሳይ በማንም የማይሰጠን ሰብዐዊ መብታችን ነው፡፡ በዚህ መብታችን ተጠቅመን ግን ወንጀል ስንፈጽም በህግ በቁጥጥር ስር በማዋል የመንቀሳቀስ ዕገዳ ሊጣልብንና እስር ቤት ልንገባ እንችላለን፡፡

በሁሉም የመብት ዓይነቶች ላይ ያለው ሀቅ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደ መንግስትና  እንደ ዜጋ መብቶቻችንን በአግባቡና በህጋዊ መንገድ ብቻ መጠቀም ብንችል ለራሳችን፣ ለወገኖቻችንና ለሀገር ያለው ፋይዳ በምንም ሊተመን የማይችል ነው፡፡ ሠላማችን እንደ ወንዝ ሞልቶ የሚፈስና ለሌሎችም የሚተርፍ ይሆናል፡፡

ስለዚህ መብቶቻችንን በህጋዊ መንገድና በህጋዊ መንገድ ብቻ በመጠቀም የህግ የበላይንት እንዲሰፍን ብሎም ሠላማችን እንዲረጋገጥ የበኩላችንን እንወጣ፡፡

የመንግስትኮሙዩኒኬሽንጉዳዮችቢሮ

 ድሬዳዋ

 11/01/2011.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here