በንግዱ ሥራዐት ላይ የህግ የበላይነት ሊሰፍን ይገባል

0
745

      መንግስት የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል ሰፊ ጥርትና ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡ ሥራ አጥነትና ድህንትን ለመቀነስ በሥራ ዕድል ፈጠራው በተለይ ወጣቶችና ሴቶችን በንቃት ያሳተፈ ሥራ እየሠራ ነው፡፡ የተንቀሳቃሽ ፈንድ በማዘጋጀት  የብድር ምችችት በማድረግ ኑሯቸውን ለማሻሻል ለሚጥሩ የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለሠራተኛው መንግስት የደረሰበትን አቅም ባገናዘበ መልኩ በተለያዩ ጊዜያቶች የደሞዝ ጭማሪ አድርጓል፡፡ጭማሪው በገበያው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ለውጥ በማጥናት ምንም ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ የማይችል መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የተደረገ ነበር፡፡

      ይሁን እንጂ ምንም ሳይቆይ የቤት ኪራይ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ በሸቀጦች ላይም ቢሆን ዋጋዎች እየጨመሩ መጥተዋል፡፡ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያልተገባና የኑሮ ውድነቱን ይበልጥ በሚያባብስ መልኩ በሸቀጦቻቸው ላይ ጭማሪ አድርገዋል ድርጊታቸው የስግብግቦች ድርጊት መሆኑን የሚያረጋግጠው መንግስት ጭማሪውን ገና ሳይተገብር ያለአንዳች ተገቢ ምክኒያት ከዕለት ወደ ዕልት የሸቀጥ ዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መገኘታቸው ነው፡፡ ይህ ድርጊት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ የኑሮ ውድነቱን በማባባስ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጥረቱና የደሞዝ ጭማሪው የታሰበለትን ዓላማ እንዳያሳካ  አንደሚያደርገው በተግባራ እየተመለከትን ነው፡፡

      ይህ ጉዳይ ከዕለት ዕለት ዋጋ ወደ ላይ ከወጣ እንዲህ በቀላሉ በማይወርድበት ሁኔታ የነዋሪውን ኑሮ በእጅጉ እየተፈታተነ ነው፡፡ስለሆነም እንደ አስተዳደርና ነዋሪ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁላችንም አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት እንዲገታ የጋራ ርብርብ ልናደርግ ይገባል፡፡

         እንደ አስተዳደሩ ነዋሪዎች የእኛን ድርሻ በመውሰድ  በትጋት ልንፈጽም ይገባል፡፡ የመጀመሪው በዕለት ተዕለት ኑሯችን የሚያጋጥሙንን ስግብግብ ነጋዴዎች ሳንሰለችና ሳንታክት በማጋለጥና ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ የሚወስዱትን እርምጃ መከታተልና ለተፈጻሚነቱ እስከመጨረሻው ከመንግስት ጎን መሆን ያስፈልጋል፡፡

ሌላውና አስተዳደራችን የኑሮ ውድነቱን ሊቀርፉ ይችላሉ በሎ በማሰብ በየቀበሌው እንዲደራጁ ያደረጋቸውን  የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራትን በአባልነት በመቀላቀልና ሙሉ ድጋፋችንን በመስጠት የሚያስፈልጉ ሸቀጦችን ከእነሱ በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ማህበራቱ የተቋቋሙለትን ዓላማ ከግቡ እንዲያደርሱ ልንተባበራቸው ይገባል፡፡ የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራት የተቋቋሙበት ዋናው ዓላማ ህብረተሰቡ በስግብግብ ነጋዴዎች እንዳይበዘበዝና  አማራጭ በማጣት እንዳይንገላታ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን ለመከላከል ነው፡፡ ይህ ዓላማ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ ለሚጎዳቸው ነዋሪዎች በሙሉ በአንድ ጥላ ስር የሚያሰባስብና የጋራ ጥቅምን በእኩልነት ለማረጋገጥ በንቃት የሚያሳትፍ ሊሆን ይገባል፡፡

              አስተዳደሩ  የህዝቡን ኑሮ ለማሻሻል የያዘው ዓላማ ግቡን እንዲመታ፤ ከዚሁ ጎን ለጎን  የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ በንግዱ ስርዓት ላይ የህግ የበላይነት የማስፈኑ  ሥራ በልዩ ትኩረት ሊሠራበት ይገባል፡፡ እኛም እንደ ነዋሪ ከመንግስት ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ ለጋራ ጥቅም ርብርባችንን አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል፡፡

ስለሆነም የጋራ ርብርባችን በአንድ ጀምበር ተፈላጊው ውጤት ሊገኝበት ስለማይችል በጽናት ያለማቋረጥ በንግዱ እንቅስቃሴ ላይ የህግ የበላይነት መስፈኑ እስኪረጋገጥ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል፡፡

የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

                                                                ድሬዳዋ

18/01/2011ዓ.ም 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here