የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የአስተዳደሩ እና የነዋሪው ህብረተሰብ ዋንኛ አጀንዳ የሆነውን መረጃ የማግኘት ፍላጎትና ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ተልዕኮ ከተሰጣቸው የአስተዳደራችን ተቋማት መካከል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አንዱና ዋንኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡

መስሪያ ቤታችን ይህንን ታላቅ ህዝባዊ አደራ ተረክቦ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የመጀመሪያው ስራ በአስተዳደሩ እየተከናወነ ያለውን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እና አፈፃፀም ለነዋሪው ህብረተሰብ በተለያዩ የኮሙዩኒኬሽን አግባቦች ተደራሽ በማድረግ እንዲሁም የህብረተሰቡን አስተያየትና አዝማሚያን ለአስተዳደሩ በማድረስ በሚያስችል መልኩ የመሰረታዊ ስራ ሂደት ለውጥ ጥናት(BPR) በማካሄድ አዲስ መዋቅርና አደረጃጀት በመፍጠር በአስተዳደሩ ቀልጣፋ፣ ፈጣንና ወቅታዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት በመዘርጋት አስተዳደሩ ደረጃውን የጠበቀና ተወዳዳሪ የሆነ አስተዳደር ለማድረግ በተደረገ ጥረት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና የአስተዳደሩን መልካም ገጽታ ለመገንባት አስፈላጊና ተገቢ የአሰራር ስርዓቶችን ቀርፆ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በመቀጠልም የአገራዊ እና የአስተዳደሩን የአምስት ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት በማድረግ የተቋማችን ተገልጋዮች/ባለድርሻ አካላት  በተቋሙ ዕቅድ ዝግጅት ገንቢ ሀሳቦችን ከማቅረብ ጀምሮ በእቅድ አፈፃፀም ግምገማ በማሳተፍ ለተግባራዊነቱ ላለፉት አምስት ተከታታይ የእቅድ አፈፃፀም ዘመን ባደረግነው ጥረት ውጤታማ ተግባራትን አከናውነናል፡፡ ለዚህም ውጤት በዋናነት ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመርና በማስፋት ጠንካራ የማስፈፀም እና የመፈፀም አቅም መገንባት መቻላችን እንዲሁም በአመራሩና በሰራተኛው ዘንድ የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር እንዲቀረፉ የአመለካት ለውጥ ለማጣትና የተቆርቋሪነት ስሜት እንዲያዳብሩ በርካታ ተግባራትን ከማከናወናችን ጎን ለጎን በተቋሙ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያደረግናቸው ጥረቶች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በቢሮአችን የለውጥ ሂደቱ ወደ ማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ከመቻሉም በላይ የተቋሙን ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላትን በአገልግሎት አሰጣጣችን ለማርካት እና አመኔታ እንዲያሳድሩ በማድረግ ረገድ ጅምር ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በቀጣይም ቢሮው በአገልግሎት አሰጣጡ የሚስተዋሉ ችግሮችን በየጊዜው በመለየት ደረጃ በደረጃ መቅረፍ፤ ቢሮው የሚሰጠውን አገልግሎት ደረጃውን የጠበቀና የተገልጋዮንና የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት መሰረት ያደረገ እንዲሆን እንዲሁም አገልግሎቱን ይበልጥ ግልጽ፤ ፍትሐዊና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ቢሮው በጽኑ ያምናል፡፡

ስለሆነም በተቋሙ የተጀመሩ የለውጥ ስራዎችን ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሁለቱን የተቋሙን አላማ አስፈፃሚዎች ማለትም የመንግስት ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ዓብይ የስራ ሂደት እና የመረጃ አካላትን የማብቃትና የማፍራት ዓብይ የስራ ሂደት ታሳቢ በማድረግ ይህ የዜጎች የስምምነት ሰነድ(Citizen’s Charter) ተዘጋጅቷል፡፡

በዚህም የዜጎች የስምምነት ሰነድ የተቋሙን ተልዕኮ፣ ራዕይ፣ እሴቶች፣ ተቋሙ የሚሰጣቸው የአገልግሎት ዓይነትና ደረጃ፣ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚጠየቁ ቅድመ ሁኔታዎች፣ የተገልጋዮች መብቶችና ግዴታዎች እንዲሁም የቅሬታ አቀባበልና አፈታት ስርዓትን አካቶ የያዘ ነው፡፡ በተጨማሪም የተገልጋዮችንም በቻርተሩ የተዘረዘሩ የቢሮውን አገልግሎቶች በምን አግባብ ማግኘት እንደሚችሉ በግልፅ የተቀመጡ ሲሆን ይህም በአንድ በኩል በመረጃ እጥረት ተገልጋዮ ከእንግልት እና አላስፈላጊ ምልልስ እንዲድን በሌላ በኩል ደግሞ በቢሮው እየተዘረጋ ያለው የተጠያቂነት አሰራር እንዲጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል፡፡