የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሐላፊ መልዕክት

ወቅቱ በፍቅር ፣ በይቅርታና በመደመር የለውጥ ጉዞ ሀገራችን ወደ አዲስ ምዕራፍ የገባችብት ወቅት ነው፡፡ ሁላችንም ከተጋባር እንዳየነው እውነተኛ ፍቅር ምን ጊዜም አሸናፊ ነው፡፡ ለሌላው ይቅርታ ማድረግና ከሌላው ይቅርታ መቀበል የብስለት ጥግ ከመሆኑም በላይ የማይደምረው አይኖርም፡፡ ይቅርታ የትኛውንም ጠብ ጸጥ የማድረግ ጉልበት አለው፡፡ ስንደመር ደግሞ አንድነታችን ይጠናከራል፡፡ አንድነት ደግሞ ምንም የማይበግረው አስተማማኝ ኃይል ነው፡፡ ለዚህም ነው እንደ ሀገር እና ህዝብ በፍቅር፣ በይቅርታና በመደመር የማንሻገረው ተግዳሮት አይኖርም ብለን በጋራ የተነሳነው፡፡

ሌላው አዲሱ የለውጥ ምዕራፍ ትሩፋት ትክክለኛውን ዲሞክራሲ ለማጎልበትና ለማስፈን  የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ መንግስት ቁርጠነቱን በተግባር ማሳየቱ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ሁሉ በለውጡ በንቃት እንዲሳተፍና ከለውጡም ተጠቃሚ እንደሆን በተደረገው ጥሪ ከሀገር ቤት እስከ ዲያስፖራ ሁሉም ተሰባስቧል፡፡ በዚህም ሁሉም የመሰለውን አስተሳሰብና የፖለቲካ አመለካከቱን ይዞ በአደባባይ በነጻነት እየተገበረ ይገኛል፡፡

ይህ በሀገራችን ታሪክ ታይቶ የማይታወቅና ዴሞክራሲያችን ወደ ሌላ የዕድገት ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡ አሁን የተያያዝነው ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን የማጠናከር ጉዞ በዚሁ ከቀጠለና በአግባባ ከያዝነው በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአስተዳደራችንን የመቻቻል የአብሮነትና እንግዳ ተቀባይነት አሴቶቻችን ጎልብተው ከመውደዳችን የተነሳ በቁልምጫ ድሬ እያልን የምንጠራት ድሬደዋን ወደ በጎ የሚለውጥ፤ እንዲሁም  ትልቅ ተስፋ እንድንሰንቅ የሚያደርግ ነው፡፡

እንደ ቢሯችን በበርካታ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር እና በጎ ገጻታችን እንዲገነባ ከህዝብ ጋር ተቀራርበን መሥራት እንፈልጋለን፡፡ በጋራ ያፈራናቸው መልካም እሴቶቻችን እንዲጠበቁና እንዲዳብሩ ብሎም ለሀገር ጥቅም እንዲውሉ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የነዋሪው የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች አድራሻቸው ታውቆ ፈጣንና ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው በአስተዳደሩና በነዋሪው መሀል ጠንካራ ግንኙነት ሊፈጠር ይገባል፡፡ የጋራ ራዕያችን የሚሳካው ስንቀራረብ እና ስንመክር ብቻ ነው፡፡

ባጠቃላይ አስተዳደሩ በማህበራዊው፣ በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ስለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴ ወቅታዊና ትክክለኛውን መረጃ ለነዋሪው በማቅረብ ንቁ ተሳታፊና የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡