በከተማችን 32 ግራም ዳቦ በ2 ብር ተሽጧል

0
153

መንግስት 100 ግራም ዳቦ በ1፡30 ሳንቲም እንዲሸጥ ከዳቦ ቤቶች ጋር ውል ቢያደርግም  በከተማዋ ያለው ዝቅተኛ የዳቦ ዋጋ 1፡50 መሆኑ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ ዳቦ ቤቶች  ግራሙን ቀንሰው ዋጋውን በመጨመር ሲሸጡም ተስተውሏል፡፡

 

“መንግስት 100 ግራም ዳቦ በ1፡30 ሳንቲም ሽጡ ብሎ ውል ሲያስገባን ዱቄት ሊያቀርብልን ታሳቢ ተደርጎ ነው” ያሉት የናቲ ዳቦ ቤት ባለቤት አቶ ታሪኩ ደጉ ናቸው፡፡

ትንሽ እርሾ ብዙ ዱቄት እንደምታቦካ ሁሉ ጥቂቶች ያጠፉትም ስህተት የሁሉንም ስም በማጉደፍ ከኑግ የተገኘ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ እየሆነብን ነው ያሉት አቶ ታሪኩ፤ መንግስት በእውነት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ቁጥጥር ማድረግና በወጣው ስታንዳርድ መሰረት የማይሰሩትን በህግ አግባብ መጠየቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በትክክል የሚሰሩትንም ደግሞ ማመስገን እንደሚገባና አቅርቦትንም ደግሞ በጊዜና በአግባቡ አሟልቶ በማቅረብ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

ገበያው ላይ ያለው የዱቄት ዋጋ እጅግ በጣም መናሩን ማንም ሰው የሚመለከተውና በዶላር ምክንያት የእያንዳንዱ እህል ዋጋ መጨመሩን እየተመለከተ መንግስት መፍትሄ ባላበጀበት ሁኔታ ግራም ቀነሳችሁ፣ ዋጋ ጨመራችሁ ተብለን ልንወቅስ አይገባም ያሉ የዳቦ ቤት ባለቤቶችም አሉ፡፡

በአስተዳደሩ ካሉ የዳቦ ቤት ባለቤቶች ጋር በንግድና ኢንደስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ አዘጋጅነት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የዳቦ ቤት ባለቤቶች፣ የዱቄት ፋብሪካዎች እንዲሁም የዱቄት አከፋፋይ ማህበራትም ተገኝተዋል፡፡ በመድረኩ ከህብረተሰቡ የሚነሱ በርካታ ቅራኔዎች በፍትሃዊ ንግድ ፅ/ቤት በኩል ቀርበው ለውይይት የቀረቡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በዋናነት የዳቦ ግራም መቀነስ፣ የጥራት ደረጃው መውረድ፣ ፍትሃዊ የሆነ የዱቄትና የስንዴ ኮታ ክፍፍል እንዲሁም የዳቦ ዋጋ ጭማሪ ይገኙበታል፡፡

ከተቋቋመ 6 አመታትን ያስቆጠረው የድሬዳዋ ዳቦ ቤቶች ማህበር ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ ረጋሣ በበኩሉ የማህበሩ ዋነኛ አላማ የዳቦ ቤቶችን ችግር ከመንግስት ጋር በጋራ በመሆን ለመቅረፍ እንዲቻል ሁኔታዎችን ማመቻቸት መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዳቦ ቤቶች ዙሪያ ያሉትን  ችግሮች በመጠቆምና የመፍትሄ አቅጣጫ በማስቀመጥ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልፀዋል፡፡

ከፌደራል መንግስት ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረው 12000 ኩንታል ዱቄት ዘንድሮ ወደ 6000 ዝቅ መደረጉም ችግር ፈጥሮ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር የገለፁት አቶ ኤርሚያስ ይህንንም ከኃላፊዎች ጋር በመነጋገር እንዲስተካከል ተደርጓል ብለዋል፡፡

የግራም መቀነስ ብቻ ሳይሆን የአቅርቦትም ማነስ ችግር እንዳለ፣ ወጥ የሆነ የስንዴ ኮታ አቅርቦት ችግር ፣ የእንጨት ችግር ፣ በየጊዜው ለሚከፈቱ ዳቦ ቤቶች የሚሆን የዱቄት ኮታ አለመጨመር ላይም ከነባሮቹ ኮታ ላይ ተቀንሶ የሚሰጥ በመሆኑ መንግስት ልብ ሊለው የሚገባ መሆኑን በቁጥጥር ስራቸው ወቅት ልየታ ማድረጋቸውን አቶ ኤርሚያስ ጠቁመዋል፡፡  የዱቄት ዋጋ በ1300 ብር በገበያ ላይ መጨመሩና ለመግዛትም ወረፋ የሚያዝ ሲሆን የስንዴ አቅርቦት የዘገየበት ምክንያት በግዢ መዘግየት መሆኑን ነው ከመንግስት የተነገረን ብለዋል፡፡ ከ50 በላይ አዳዲስ ዳቦ ቤቶች ወደ ማህበሩ አባልነት ባልመጡበት ሁኔታ ማህበሩ ለቁጥጥር ስራ እንደሚቸገርም አቶ ኤርሚያስ ተናግረዋል፡፡

የአያን ዱቄት ፋብሪካን ወክለው የመጡት አቶ ሱሌማን በበኩላቸው ፍትሃዊ የሆነ የስንዴ ክፍፍል እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሉት ከዚህ ቀደም 1200 ኩንታል ስንዴ ለፋብሪካቸው ይሰጥ እንደነበርና ይህም ቀንሶ 200 ኩንታል እንደሆነ አሁን ላይ እየተሰጣቸው ያለው በመግለፅ፤ በዚህ ሁኔታ ዱቄት ፈጭቶ በበቂ ሁኔታ ለደንበኛ ማቅረብ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ አስተዳደሩ ይህንን አሰራር በማስተካከል ለሁሉም የዱቄት ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን ከሚዛን ውስጥ በማስገባት ፍትሃዊ የሆነ የስንዴ ኮታ ክፍፍል እንዲያደርግ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በዋናነት የችግሩ መነሻ የሆነው ለአስተዳደሩ ከዚህ ቀደም ከ19,299 ኩንታል በላይ ስንዴ ይገባ የነበረበት ሁኔታ እንደነበር ጠቁመው፤ በዚህ አመት ግን ይሄ መጠን ከግማሽ በላይ በመቀነስ ወደ 9,649 ኩንታል መውረዱ ነው ብለዋል፡፡ ድሬዳዋ የስንዴ ምርት አምርታ ያላትን ነዋሪ ማዳረስ የሚችል ዱቄት ማምረት የማትችል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፌደራል መንግስትና ከተለያዩ የክልል ማህበራቶች ጋር በመነጋገር አሁን ላይ በቂ የሆነ ስንዴ ሀገር ውስጥ እየገባ መሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው በማህበረሰቡ ላይ ብዝበዛ የሚያደርጉና ደሀውን ማህበረሰብ የዳቦ ግራም በመቀነስና ዋጋ በመጨመር መንግስት ላይ እንዲያምጽ በሚያደርጉ ዳቦ ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የህግ የበላይነትን እንዲያውቁ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here