ህብረተሰቡ ግብሩን በአግባቡ እንዲከፍል የሀይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

0
103

በድሬደዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን በተከናወነው የታክስ ንቅናቄ መድረክ ተገኝተው ለንግዱ ማህበረሰብ ግብርን በአግባቡ አለመክፈል በምድርም በሰማይም እንደሚያስጠይቅ ያስተማሩት  የሀይማኖት አባቶች ግብርን በመክፈል ሁሉም ዜጋ ለሀገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 30 የደረጃ 3 (ሐ) ግብር ከፋዮች ግብራቸውን የሚከፍሉበት ወቅት በመሆኑ ሁሉም ግብር ከፋይ በወቅቱ ግብሩን እንዲከፍል ያሣሠቡት የድሬደዋ አስተዳደር ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሐመድ  ህብረተሰቡ ግብሩን ሳይከፍል ቆይቶ ወሩ ሲገባደድ በወረፋ መንጓተት አልፎ ተርፎም ለቅጣት እንዳይዳረግ ከወዲሁ አሳስበዋል፡፡

አቶ ካሊድ አክለውም እንደ  ሀገር ቆመን ለመቀጠል ወሳኝ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ ግብርን መክፈል አንዱ ነው ያሉ ሲሆን ግብርን ከመሰወር ፣ ከመደበቅና ከአቅም በታች ከማሳወቅ ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በጋራ መከላከልም ይገባል ብለዋል፡፡

በወቅቱ በመድረኩ ላይ አግኝተን ያነጋገርናቸው ግብር ከፋዮች ግብርን መክፈል የሀገርን ልማት ማፋጠን በመሆኑ ዞሮ ዞሮ በልማቱ ተጠቃሚዎች እኛውና ቤተሰባችን በመሆናችን ይሄ ገብቶንና ደስ ብሎን ነው ግብር የምንከፍለው ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይም ግብርን በወቅቱና በታማኝነት ለመክፈል የቃል መግባት ስነ ሥርዓት የተካሄደ ሲሆን የታክስ አምባሳደሮችም በታክስ ዙሪያ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here