የክረምት በጎ ፍቃድ ስራው በይፋ ተጀምሯል  በበጎ ፍቃድ ስራው – 60 ሺ ወጣቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከ55 ሚሊየን ብር በላይ ማትረፍ ይቻላል፡፡

0
161

     በዘንድሮ አመት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ጥሪ መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ 4ሚሊየን ያህል ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል፡፡ ከዚህም ውስጥ አስተዳደራችን ድሬዳዋ 250 ሺ ያህሉን ችግኞች በመትከል የድርሻዋን ሚና ለመወጣት ዱላ ቅብብሎሹን ጀምራለች፡፡

 

     በመላው አለም ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ በሚከሰቱ የካንሰርና የመተንፈሻ አካላት በሽታዎች በየአመቱ 7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ወይም በየአንድ ሰዓቱ 800 ያህል ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታውቋል፡፡

     በአለማችን ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ አገራት ዜጎች ጤናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል የተበከለ አየር እንደሚተነፍሱ የጠቆመው ተመድ፣ ከሰላሳ በመቶ በላይ ያህሉም ህጻናት መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡ ከአለማችን ህዝብ 90 በመቶው ለአየር ብክለት የተጋለጠ እንደሆነ ያመለከተው ሪፖርቱ፣ 93 በመቶ የአለማችን ህጻናት የአለም የጤና ድርጅት ካስቀመጠው የአየር ብክለት ደረጃ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩና በየአመቱ 600 ሺህ ያህል ህጻናት በአየር ብክለት ሳቢያ ካለጊዜያቸው እንደሚሞቱም ገልጧል፡፡

     በመላው አለም በየአመቱ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በወባ፣ በሳንባ ነቀርሳና በኤች አይ ቪ ኤድስ ሳቢያ ከሚሞቱት አጠቃላይ ሰዎች ቁጥር በሶስት እጥፍ ያህል እንደሚበልጥም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

     ይህንን ታሳቢ ያደረገችው አገራችን ኢትዮጲያ ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ የክረምት የበጎ ፍቃድ ስራን በማከናወን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡

    በከተማችን ድሬዳዋም ይህንኑ ውጥን ለማሳካት ከ60 ሺ በላይ የአስተዳደሩን ወጣቶች በማስተባበር  በከተማዋ ልዩ ልዩ ቦታዎች ችግኞችን የመትከል ስራዎች ስታካሂድ ቆይታለች፡፡

      የከተማዋ ወጣቶች የኦሎምፒክ ሳምንት ማጠቃለያ አስመልክቶ በአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ችግኞችን የተከሉ ሲሆን በከተማዋ በሶስት ቀጠናዎች በመከፋፈል የጅምናስቲክ ስፖርታዊ ትርኢቶችን በጎዳናዎች ላይ አሳይተዋል፡፡

     የድሬዳዋ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አና ዑመር በበጎ ፍቃድ ማስጀመሪያና የኦሎምፒክ ሳምንት ማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ እንደተናገሩት በክረምት መርሃ ግብሩ ላይ በ7 አገልግሎት ዘርፎች በመሰረታዊነት ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም ይከናወኑ ከነበሩት የአረጋውያንን ቤት ማደስ፣ ደም ልገሳ፣ ችግኝ ተከላ፣ የስፖርት ውድድር፣ የማጠናከሪያ ትምህርትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ከማዘጋጀት ጎን ለጎን የዚህን አመት ለየት የሚያደርገው በትምህርት ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን እንዲሁም የኪነጥበብ ባለሞያዎችን በማጣመር ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በጋራ በመሆን ተማሪዎች ክረምትን በንባብ እንዲያሳልፉ የመፃህፍት ድጋፍ መደረጉንና መሰረታዊ የሳይንስ ትምህርቶች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ገልፀው፤ ስለ ሰላምና ፀጥታ ጉዳይም ከወጣቱ ጋር ለመምከር የተለያዩ መድረኮች እንደሚኖሩም ተናግረዋል፡፡

     በእለቱ 2000ሺ ችግኞች በአስተዳደሩ ኮንጎ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ተተክሏል፡፡ በክረምት በጎ ፍቃድ ስራው በወጣቶች የሚሰራው ስራ አሁን ገበያ ላይ ባለው ዝቅተኛ የጉልበት ተመን ዋጋ ሲተመን አስተዳደሩ ሊያወጣ ካሰበው 55 ሚሊየን ብር ወጪ ያድነዋል ተብሏል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here