መጪውን ክረምት ከመፃህፍት ጋር ለማሳለፍ የሚያግዝ የንባብ ሣምንት ተከበረ  የማይጠቅም ባህልን በማስወገድ፣ የሚበጀንን በማስቀጠል፣ መልካምን መልመድ ይገባል ተብሏል፡፡

0
130

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃሐፍት ኤጀንሲ ከድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት እንዲሁም ከድሬዳዋ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀው “ክረም  ተ መፃህፍት በአንባቢዋ ድሬ” የንባብ ሣምንት በተለያዩ ዝግጅቶች ታዋቂ ደራሲያንና የኪነ-ጥበብ ሰዎች በታደሙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሮ ውሏል፡፡ አውደ ርዕዩ በድሬዳዋ አስተዳደር ሲከበር ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

 

ባሳለፍነው ሳምንት በአስተዳደራችን ድሬዳዋ ምድር ባቡር አደባባይ በተዘጋጀው የመፅሐፍ ሽያጭ ላይ የታደሙ በርካታ አንባቢያን መፅሐፍቶችን በመግዛትና በባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ለጉብኝት የቀረቡትን የተለያዩ ቅርሶች፣ ኢትዮጵያ በአለም ቅርጽነት በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን 12ቱ የጽሁፍ ቅርፅ እንዲሁም የተለያዩ የህትመት ውጤቶች እና ፎቶዎች ጎብኝተዋል፡፡

የፕሮግራሙ አዘጋጅ የድሬዳዋ አስተዳደር የባህልና ቱሪዝም ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ በመክፈቻ ስነ ስርኣቱ ላይ ተገኝተው ለእንግዶች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ንባብና ድሬዳዋ የማይነጣጠል ታሪካዊ ቁርኝት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ማሣያ የሚሆኑት ቀደምት ማተሚያ ቤቶች በከተማዋ ውስጥ መኖራቸው መሆኑን በመጠቆም፡፡

አቶ ሙራድ በማከልም ነባር የማይጠቅመንን ባህል በማስወገድ ቀደምት የሚበጁንን አኩሪ ባህሎች በማስቀጠል፣ ሌሎች አዳዲስና መልካም የሆኑ ባህሎችን በመላመድ ህብረተሰባችን በተለይም ተተኪ ህፃናትና ወጣቶች በመልካም ስነ-ምግባር ሊያድጉ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ መጪውንም ክረምት ተማሪዎች በቤታቸውም ይሁን በቤተ መፃህፍት መፃህፍትን የማንበብ ባህል እንዲያዳብሩና መፃህፍትንም እንዲገዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ይኩኑአምላክ መዝገቡ ለድሬዳዋ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ክረምት በንባብ እራሳችሁን በተለያዩ እውቀቶች የምትገነቡበት እንዲሆን በማሰብ የተለያዩ የኪነጥበብ ሰዎችና ደራሲዎችን ይዘን መጥተናል፡፡ ከእነሱም በምታገኙት የንባብ ተሞክሮ በመማር ብዙ አንባቢያንና ፀሐፊዎችን ማፍራት እንደሚቻል ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡

በሣምንቱ በተዘጋጁት መድረኮች ላይ በመገኘት ለተማሪዎችና ለኪነ ጥበብ ሰዎች እንዲሁም በየቀበሌው ለሚገኙ ባለሞያዎች ያላቸውን ተሞክሮ ያቀረቡት ደራሲ ዘነበ ወላ እና ደራሲት እሴተ ታደሰ ተማሪዎች ክረምትን ከመፅሐፍ እንዲከርሙ ምክራቸውን በመለገስ በንባብ ያላቸውንም ልምድና የሕይወት ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡

በዝግጅቱ ታዳሚ የነበሩ የኪነ-ጥበብ ሰዎችና ተማሪዎችም እንዲህ አይነት መድረክ መዘጋጀቱ የተዳከመውን የንባብ ባህላችንን ለማነቃቃት አይነተኛ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here