ህብረተሰቡ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉን በማዳበር የአገሪቷን ገቢ በማሳደግ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

0
112

«ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ»  በሚል መሪ ቃል ከግንቦት 18 እስከ ሰኔ 16/2011 ዓ.ም ለአንድ ወር በተለያዩ ዝግጅቶች በአስተዳደሩ የተከበረው የታክስ ንቅናቄ ውጤታማ እንደነበር ተገለፀ፡፡

 

በድሬደዋ አስተዳደር የገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ካሊድ መሀመድ ለአንድ ወር ሲካሄድ የቆየው የታክስና የገቢ ንቅናቄ፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በፓናል ውይይቶች እንዲሁም በመስክ ጉብኝቶች መከበሩን ገልፀዋል፡፡

የታክስ ንቅናቄው ለአንድ ጊዜ ብቻ ተካሂዶ የሚቀር ሳይሆን በቀጣይ ከባንኮችና ከሴክተር ግብር ከፋይ መስሪያ  ቤቶች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት  ገቢን ለማሳደግ አሠራሩን ለማሻሻል ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ከመረጃ አያያዝ ጋር ሰፊ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ካሊድ ገልፀዋል፡፡

በታክስ ንቅናቄው ሂደት ከባለድርሻ አካላት ጋር መንግስትና ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ እንዴት ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት በመነጋገራችን ወደፊት ባሉት ጊዜያት ማህበረሰቡ ውስጥ ገብተው የጀመሩትን ስራ እንዳያቋርጡና ግብር ከፋዩን እንዲያነቃቁ ተልዕኮ መሰጠቱን አቶ ካሊድ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአስተዳደሩ ከ20.000 በላይ ግብር ከፋዮች እንዳሉ የገለፁት ዳይሬክተሩ ምንም እንኳን በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥሙም በአስተዳደር ደረጃ ገቢ የመሰብሰብ አቅማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በ1998 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ለመሰብሰብ የተቻለው አመታዊ ገቢ 53 ሚሊዮን ብር እንደነበርና በ2011 ዓ.ም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ በ10 ወራት አፈፃፀም ብቻ 987 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ  መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ሐምሌ ወር ደረጃ 3 የግብር ከፋዮች የሚከፍሉበት ወቅት በመሆኑ በአግባቡ ለማስተናገድ አደረጃጀቱን በመፈተሽ  ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን በመጠቆም ከግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ጋር በመወያየት በአካባቢ በመከፋፈል እና አሸዋና ሳቢያን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን በማጠናከር አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት እያደረግን በመሆኑ የመጨረሻ ቀን ያለውን መጨናነቅ ያቀለዋል  ብለዋል፡፡

አቶ ካሊድ ለማህበረሰቡ ባስተላለፉት መልዕክት ማንኛውም ህብረተሰብ ግብይት ባካሄደበት ቦታ ደረሰኝ የመጠየቅ ባህሉን በማዳበር የአገሪቷን ገቢ በማሳደግና ብልሹ አሠራሮችን በመጠቆም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ፡፡

ግብር ከፋዩ ለድሬደዋ ስልጣኔ የሚከፈል አድርጎ በማሰብ ደረሰኝ በመቁረጥና ከግብር ማጭበርበር በመፅዳት እንዲሁም  የሂሳብ መዝገቡን ገቢና ወጪ በመመዝገብ ግብር  በአግባቡ እንዲከፍሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአስተዳደሩ ያሉትን ትክክልና እውነተኛ  ግብር ከፋዮች በቀጣይ እውቅና ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም አቶ ካሊድ ጠቁመዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here