ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች እየተገነቡ ናቸው

0
350

ድሬዳዋን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴውን የሚያጎለብቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በወጣባቸውየጌጠኛ ጡብ ድንጋይ መንገዶች እየተገነቡ መሆናቸውን የከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት ገለፀ፡፡

     በአብዛኛው ተጠናቀው አገልግሎት የጀመሩት መንገዶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ማህበራዊ ኑሮን በማጎልበት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የመንገዱ ተጠቃዎችና ገንቢዎች ተናግረዋል፡፡

     የድሬዳዋ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የልማት ዕቅድ አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ እንደገለፁት በአስተዳደሩና ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር አምናና ዘንድሮ 20 ኪሎ ሜትር የጡብ ድንጋይ መንገዶች በዘጠኙ ቀበሌዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡

     በ42.6 ሚሊዮን ብር አምና የተጀመሩትና ወደ ዘንድሮ የተሸጋገሩት መንገዶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው የህብረተሰቡን ማህበራዊ ኑሮና መስተጋብር እያሻሻሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

     ዘንድሮም በ30 ሚሊዮን 2 መቶ ሺ ብር 8 ኪሎ ሜትር መንገድ መልካ ጀብዱን ጨምሮ በሁሉም ቀበሌዎች እየተገነቡ መሆናቸውን ነው አቶ ኤፍሬም ያስታወቁት፡፡

       አምናና ዘንድሮ እየተገነቡ በሚገኙት የጌጠኛ ጡብ ድንጋይ መንገዶች ላይ 6 መቶ አባላት ያሏቸው 60 የድንጋይ ጠራቢና አንጣፊ ማህበራት የሥራ እድል ማግኘታቸውን ገልፀዋል፡፡

       በመንገድ ፕሮጀክት ላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ስኬት የድንጋይ አንጣፊ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ሙህዲን ሰማን 10ሩ የማህበሩ ወጣት አባላት ያገኙት የሥራ ዕድል የራሳቸውንና የቤተሰባቸው ህይወት እንዲለውጡ ማገዙን ተናግረዋል፡፡

       ‹‹የማህበሩ አባላት በቆጠብነው ገንዘብ ላይ ብድር ወስደን በዳቦ መጋገር ሥራ ለመሰማራት ተዘጋጅተናል፤ ሥራውን ለመጀመር እየጠበቅን ያለነው የመስሪያ ቦታ ጥያቄያችንን ምላሽ ብቻ ነው››ብለዋል፡፡

     መንገዶቹ የሳቢያንን አዋራማና ለጤና ጠንቅ የሆኑ ሥፍራዎችን ለውጠዋል፤ ልጆችና አዛውንቶች እንደልባቸው መጓዝ አስችለዋል፣ የታክሲ አገልግሎትም በተፈለገ ጊዜ ለማግኘት እንችላለን ያሉት የሳቢያን ቀበሌ ነዋሪ ወ/ሮ አዚዛ በክሪ ናቸው፡፡

         ተመሳሳይ ሃሳብን የገለፁት የገንደ ቆሬ ነዋሪ አቶ ደምስ አየለ፤ ‹‹አይነ ስውር ነኝ፤መንገዱ ሳይሰራ የተለያዩ ቦዮች ውስጥ በመግባት ለጉዳት ስዳረግና በሰው ድጋፍ ስመራ ነበር፤ አሁን ግን እንደልቤ ያለማንም ድጋፍ ወጥቼ እገባለሁ›› ብለዋል፡፡

     የመልካ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ ሁሴን በበኩላቸው በቀበሌው የጡብ ድንጋይ የተዘጋጀ ቢሆንም መንገዱ በሚፈለገው ፍጥነት እየተሰራ ባለመሆኑ ሥራው በፍጥነት እንዲከናወን ክትትል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡‹‹ ቀደም ሲል የተገነቡት በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሰበብ ፈርሰው አልተጠገኑም፤ አሁን የሚገነቡትም እንዳይፈርሱ መከላከል ይገባል ›› ብለዋል፡፡

       የከተማው ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት የልማት ዕቅድ አስተባባሪ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ቀደም ሲል ሲፈጠር የነበረው የቅንጅት ችግር ለመፍታት የሚያስችል ውል በመሠረተ ልማት ከዋኝ ተቋማት መካከል መፈረሙን ተናግረዋል፤ የሚፈርሱ መንገዶች በፍጥነት የሚሰሩበት አሠራር መቀየሱንም ጠቁመዋል፡፡

       በሀገራችን የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ሥራ በ1997 ዓ.ም. በድሬዳዋ የተጀመረ ሲሆን ይህ ተሞክሮ በአሁን ሰዓት በመላው ሀገሪቱ ከተሞች መስፋፋቱ ይታወቃል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here