ወጣቱ በምክኒያት ሊደግፍ በምክኒያት ሊቃወምና ሊያወግዝ ይገባል

0
410

በዓለማችን ያሉ ምሁራን አሁን የምንገኝበት ዘመን የመረጃ ዘመን እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ በእርግጥም እጅግ በዘመኑና ከዚህ በፊት ባልነበሩ የቴክኒዮሎጂ ውጤቶች በመታገዝ  መረጃዎች ሊገመት በማይችል ፍጥነት ከዓለማችን አንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየደረሱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ በጣም ግዙፍና ሰፊ የሆነችው ዓለማችን ወደ አንድ መንደር ተቀይራለች፡፡

መረጃ ትልቅ ሀብት መሆኑን ዓለም በተግባር አስኪመለከት ድረስ መረጃዎች ከምንጊዜውም በላይ የኑሮ ዘይቤያችንን እየቀየሩት ነው፡፡ ይሄ መሆኑ በትክክለኛ መረጃዎች የበለጸገና ኑሮን በቀላሉ መምራት የሚችል ስልጡን  ሀገራዊ መግባባት ላይ የደረሰ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ትክክል ያልሆኑና ሁን ተብለው ለአንድ እኩይ ዓላማ ማሳኪያ ተፈብርከው የሚሰራጩ መረጃዎች የተወዛገበና ከሀገራዊ መግባባትና አንድነት በተቃራኒው የሚቆም ማህበረሰብ እየፈጠሩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተለይም ፌስቡክና ዩትዩብ በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ወጣቱ ከሚያገኛቸው መረጃዎች በመነሳት ወደ ውሳኔና ተግባር ከመግባቱ በፊት ቆም ብሎ ይህን ጉዳይ በአንክሮ ሊያስብበትና የመረጃዎችን ተገቢነትና ትክክለኛነት ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቁ መረጃዎች ዘመኑ ባመጣቸው ቴክኒዮሎጂዎች በመታገዝ የተንቀሳቃሽ ምስልን፣ የምስልንና የጽሁፎችን ይዘትና ቅርጽ በመቀየር ለእኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያነት እንደሚውሉ በተጨባጭ እያየናቸው ነው፡፡

እነዚህ የተፈበረኩ መረጃዎች በግብታዊነት የሚቀበሏቸውንና የሚጠቀሙባቸውን ማንንም ቢሆን ስሜታዊ እንዲያደርጉ ሁን ተብለው የተዘጋጁ ስለሆነ ወጣቱ በሰከነ አእምሮና በተረጋጋ መንፈስ ሊመረምራቸው ይገባል፡፡ ወጣቱ ስለእያንዳንዷ መረጃ አጥብቆ ጠያቂና በተረጋገጡ ምክንያቶች ብቻ ደጋፊና ነቃፊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡

ዛሬ ያለበቂና አሳማኝ ምክኒያት የደገፍነውም ሆነ የነቀፍነው ጉዳይ ከራሳችን አልፎ የጋራችን የሆነችውን ይህችን መተኪያ የሌላት ሀገር ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ልብ ልንል ይገባል፡፡ ሀገር ተረካቢና ያለፈው ትውልድ ተስፋዎች ነን ብለን ካመንን በተሳሳቱ ወሬዎች ምክኒያት የፈራረሰች ሀገር መረከብ የለብንም፡፡ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ነውና ብሂሉ፡፡

ኃላፊነት በተሞላበት ስሜት መረጃዎችን እንቀበል፤ እንጠቀም፤ ለሌላውም እንስጥ፡፡ በበቂ ምክኒያቶች እንደግፍ፡፡ በበቂ ምክኒያቶች እንንቀፍ፡፡ ይህን ስናደርግ ለሀገራዊ መግባባት ምትክ የሌለው ሚና የሚጫወት፣ በተፈበረኩ መረጃዎች የማይናወጥ ፣ ለምንም የማይበገርና ተስፋ የሚጣልበት  አንድ ትኩስ ኃይል እንሆናለን፡፡

የመንግስትኮሙዩኒኬሽንጉዳዮችቢሮ

ድሬዳዋ

14/12/2010 .

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here